በእግር ኳሱ የተፈጠረው ክፍፍል የተነቃቃውን እግር ኳስ እንዳያደበዝዘው ሥጋት ፈጥሯል

Image

-አገልግሎቱን ያጠናቀቀው አመራር ለፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዳይሬክተር ሾመ

የኢትዮጵያን እግር ኳስ ፌዴሬሽን እያስተዳደረ የሚገኘው የአቶ ሳሕሉ ገብረወልድ ካቢኔ፣ የአገልግሎት ዘመኑ ሊያበቃ የአንድ ወር ዕድሜ ቀርቶታል፡፡

ካቢኔው ምንም እንኳ የአገልግሎት ዘመኑን እያጠናቀቀ ነው ተብሎ ቢታመንም ባለቀ የሥልጣን ዘመኑ እየተፈጠረ ባለው የአሠራር ክፍተት ምክንያት ክፍፍል መፈጠሩም እየተሰማ ነው፡፡

የፌዴሬሽን ምንጮች ለሪፖርተር እንደሚገልጹት ከሆነ፣ በአቶ ሳሕሉ ካቢኔ መካከል ለተፈጠረው ክፍፍል መንስኤው አንዱ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ፌዴሬሽኑ ‹‹ያሬድ ኮንትራክተር›› ለተባለ ድርጅት ያለ ጨረታ ሰጠው በተባለው 1.3 ሚሊዮን ብር (74 ሺሕ ዶላር) ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡

ሌላው የሚሉት ምንጮቹ፣ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ሳሕሉ ከካቢኔያቸው ጋር ሳይመክሩ ለአገር አቀፉ ስፖርት ምክር ቤት፣ የ2019 እና 2021 የአፍሪካ ዋንጫ በኢትዮጵያ እንዲዘጋጅ ሐሳብ ማቅረባቸው፣ በመገንባት ላይ የሚገኘው የሐዋሳ ስታዲዮም የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) በሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ሰው ሠራሽ (አርቴፊሻል) ሳር እንዲለብስ ዕቅድ ማስያዛቸው፣ የመጨረሻውና በአመራሩ መካከል ለተፈጠረው ልዩነት መባባስ ዓይነተኛ ምክንያት ደግሞ፣ አመራሩ የአገልግሎት ዘመኑን እያጠናቀቀ መሆኑን እያወቀ፣ ‹‹እኔ ከሞትኩ…››፣ ዓይነት በእግር ኳስ ቤተሰቡ ዘንድ እምነትና ተአማኒነት ያጡ ሰዎችን ሹመት ማፅደቅ ‹‹አለብን፤ የለብንም›› የሚለው ተጠቅሷል፡፡

ፀረ ሙስና ኮሚሽን የጠየቀውን ማብራሪያ በተመለከተ አመራሩ፣ ባለፈው ዓርብ ኡራኤል አካባቢ በሚገኘው በዲ ሊ ኦፓል ሆቴል ባደረገው ስብሰባ አቶ ሳሕሉ በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ‹‹ሥራ አስፈጻሚው አይመለከተውም›› ማለታቸው ተገቢ እንዳልሆነ በማመናቸው አመራሩን ይቅርታ ጠይቀው፣ ፀረ ሙስና የጠየቀውን ማብራሪያ ጉዳይ ለመወሰን፣ (በሕትመት ምክንያት በዚህ ዘገባ ባናካትተውም) ትናንት ነሐሴ 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ስብሰባ ተቀምጧል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅትና የሐዋሳውን ስታዲየም ሰው ሠራሽ ሳር የማልበስ ጥያቄን በተመለከተም በተመሳሳይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ባቀረቡት ይቅርታ እንዲታለፍ ተደርጓል ተብሏል፡፡ አንዳንድ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ግን ‹‹ይቅርታው እስከምን ድረስ?›› በሚል ጥያቄ በማንሳታቸው ‹‹በልዩነት ተጠናቋል›› ተብሏል፡፡

ይሁንና እንደ ምንጮቹ፣ የአገልግሎት ዘመኑን እያጠናቀቀ ያለው ካቢኔ በመጨረሻው ሰዓት በነበረው የሥራ ዘመን ከአመራሩ ጋር ቅርበት ያላቸው፣ ነገር ግን ደግሞ በእግር ኳስ ቤተሰቡም ሆነ በሙያተኞች ዘንድ በሙያ ብቃታቸው የማይታመንባቸውን ሰዎች ሹመት ለማፅደቅ የቀረበው ሐሳብ ክርክር መፍጠሩ ነው፡፡

የልዩነቱ መነሻ ሐሳብ፣ ከአመራሩ አንዳንዳቹ፤ ‹‹እኛ በመጥፎም ይሁን በስኬት የአገልግሎት ዘመናችንን ጨርሰናል፡፡ ፌዴሬሽኑን በአዲስ የሚረከበው አመራር ከዚህኛው የወሰደውን ጠንካራና ደካማ ጎን አይቶና መርምሮ፣ ለአገሪቱ እግር ኳስ ይጠቅማል የሚለውን ሙያተኛ አወዳድሮ በሚመለከተው ቦታ እንዲያስቀምጥ ዕድል ልንሰጠው ይገባል፡፡ ይህ መሆን ሲገባው ባለቀ ሰዓት እኛ ያስቀመጥንለትን ሰው ይዞ እንዲቀጥል ማድረግ አይገባም፤›› የሚሉ በአንድ በኩል ሲኖሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ስንጀምር ጀምሮ እኛን በታማኝነትና በፅናት ሲያገለግሉ የቆዩ ሰዎች በቀጣይ የሚጠብቃቸውን ሳናመቻችላቸው ዝም ብሎ መውጣት አይገባም፤›› የሚሉ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በመጨረሻም በትናንቱ ስብሰባ የአገልግሎት ዘመኑን እያጠናቀቀ ላለው አመራር ‹‹በታማኝነትና በፅናት ሲሠሩ ቆይተዋል›› ከተባሉት ውስጥ አቶ መኮንን ኩሩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር ሆነው እንዲቀጥሉ በድምፅ ብልጫ ተመርጠዋል፡፡

በእግር ኳሱ አመራር መካከል እየተፈጠረ ያለውን ትርምስ አስመልክቶ ያነጋገርናቸው አንዳንድ ሰዎች፣ ‹‹ማንነታችን ገልጸን ብንናገር የምናተርፈው ቂም እንጂ ውደሳን ስላልሆነ ቢቀርብን›› ሲሉ ዝምታን መርጠዋል፡፡

ይሁንና ማንነታቸው እንዳይገለጽላቸው የፈለጉ አንዱ የሰጡን መልስ ግን ‹‹ክፍፍሉ የቆየውን ኔትዎርክ እናፍርስ አናፈርስም ነው፡፡ ፈረሰ ማለት ደግሞ በቀጣይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ አቅምና ብቃቱ ባላቸው ሙያተኛ ሊመራና የተነቃቃው እግር ኳስ ወደተሻለ ደረጃ ሊሸጋገር ነው፡፡ እንነጋገር ከተባለ የአገሪቱ እግር ኳስ በዘርፉ ክህሎቱ ያላቸው ወጣቶች ድህነት የለበትም፡፡ ድህነቱ በእከክልኝ ልከክልህ የተጠላለፈው አሠራር ባለ ክህሎቶቹን ታዳጊዎች ተመልካች እንዳይኖራቸው ማድረጉ ነው፤›› ብለው፣ የሚመለከተው አካል፣ እንደዚህ ዓይንና ጥርስ አውጥቶ እያከራከረ ያለውን ጉዳይ አበክሮ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጭምር ጠይቀዋል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s